ስለ ፌደራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን

የኢፌዲሪ ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀፅ 86 የተቋቋመ ሲሆን ኮሚሽኑ ከተቋቋመለት አበይት ተግባራት አንዱና ዋነኛዉ የታክስ ከፋዩን ማህበረሰብ አቤቱታ ተቀብሎ የግራ ቀኙን  በማድመጥ የዉሳኔ አሰጣጥ ሂደት ተደራሽ ፍትሀዊ ፣ ፈጣን ፣ ዉጤታማ ፣ ግልፅነት እና ተጠያቂነት ያለዉ እንዲሆን በማድረግና የታክስ ከፋዩን ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ግብር ያለአንዳች ቅሬታ በመክፈል አገሪቱ ለጀመረችዉ የለዉጥ ጉዞ የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክትና በታክስ ሂደቱ ቅር የተሰኘበት ጉዳይም ሲያጋጥም በአፋጣኝ መፍትሄ እንዲያገኝ መንግስት በገለልተኛ አካል በኮሚሽን ደረጃ እንዲቋቋም ተደርጎ በርካታ አበረታች ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ 

ከታክስ ጋር ተያይዞ ይግባኝ ለማለት መታወቅ ያለባቸዉ ጉዳዮች

ይግባኝ ባይ ለፌደራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ይግባኙን ግልፅ በሆነ ማመልከቻ ማቅረብ ያለበት ሲሆን የውሳኔ ማስታወቂያ ከተቀበለ ጀምሮ 30 ቀን ያላለፈው ፣ አከራካሪ የሆነው የገንዘብ መጠን የገቢዎች ጉዳይ ከሆነ 5ዐ% ፣ የጉምሩክ ጉዳይ ከሆነ 1ዐዐ% የተከፈለበት ደረሰኝ ፣ ለጉዳዩ በማስረጃነት የሚያገለግሉ አባሪ ሰነዶች ፣ የሥር አቤቱታ አጣሪ ውሳኔ ፣ የንግድ ሥራ ፈቃድ ፣ የንግድ ምዝገባ ሰርተፊኬት ፣  የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ የምስክር ወረቀት ፣ መተዳደሪያ ደንብ ፣ መመስረቻ ጽሁፍ በእንግሊዝኛ ከሆነ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ ከይግባኙ ጋር መቅረብ ይኖርበታል::

ይግባኝ የሚያቀርበዉ አካል ይግባኝ ማለት የሚችለዉ በሁለት አይነት መልኩ ሲሆን አንደኛ በገቢዎች ወይንም በጉምሩክ ጉዳይ ኖሮት ለጉዳዩ በሁለቱ አካላት የመጨረሻ ውሳኔ የተሰጠው እና በ30 ቀን ጊዜ ውስጥ የቀረበ ከሆነ ሁለተኛ ከ30 ቀን በኋላ ዘግይቶ ለሚመጣ የዘገየበት ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት መሆኑን ማስረጃ አቅርቦ እንዲፈቀድለት የሚጠይቅ ከሆነ እና ከተፈቀደለት ይግባኝ ይከፈትለታል፡፡ ይግባኙ መቅረብ ያለበት በባለቤት ፣ በስራ አስኪያጅ ወይንም በህጋዊ ወኪል/በጠበቃ/ ሲሆን ውክልናው በውልና ማስረጃ የተረጋገጠ ወይም መ/ቤቱ ለተጠየቀው ግብር በተመለከተ መከራከሩን የሚገልጽ ውክልና በዋናው ሥራ አስኪያጅ መወከሉን በማኀተም ተረጋግጦ የሚያቀርብ መሆን አለበት፡፡

ራዕይ
ፍትሐዊ የግብር ውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓት ተፈጥሮ ማየት።

ተልዕኮ
ህግንና አሰራርን መሰረት በማድረግ የህግ የበላይነትንና ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ፍትሐዊ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ ተደራሽ የሆነ የታክስ ውሳኔዎችን መስጠት።

  • እሴቶች
  • ግልፀኝነት
  • ተደራሽነት
  • ነፃነት
  • ተጠያቂነት
  • ውጤታማነት
  • ፍትሐዊነት
  • ብቃት